በስኳር ኢንደስትሪ የኮሮና ቫይረስን/COVID-19 ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ቀጥሏል

በስኳር ኢንደስትሪ የኮሮና ቫይረስ በሽታን/COVID-19 ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ በስኳር ኮርፖሬሽን ዋና መ/ቤት፣ በስኳር ፋብሪካዎችና ፕሮጀክቶች በተቋቋሙ አብይና የቴክኒክ ኮሚቴዎች መሪነት ወረርሽኙን ለመከላከል ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል፡፡

በተለይም በርካታ ሠራተኞች በሚገኙባቸው የስኳር ፋብሪካዎችና ፕሮጀክቶች የቫይረሱን ሥርጭት በተቀናጀ ሁኔታ ለመከላከል እንዲቻል በአካባቢዎቹ ከሚገኙ ማኅበረሰቦች፣ አጋር የልማት ድርጅቶች እንዲሁም ከወረዳ መስተዳድሮች ጋር ጥምረት በመፍጠር ሥራዎችን በጋራ ለመፈጸም የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎች በመደረግ ላይ ናቸው፡፡

ስኳር ኮርፖሬሽን ከጤና ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እንዲሁም መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ የጤና ተቋማት ጋር በፈጠረው ግንኙነት ለጤና ባለሙያዎች ሥልጠናዎችን ከማመቻቸት ባሻገር የተለያዩ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችንና የመከላከያ ግብዓቶችን ለማሰባሰብ ችሏል፡፡

ከዚህ ባሻገር ከመጋቢት 8/2012 ዓ.ም አንስቶ ወደ ሥራ የገቡት የኮርፖሬሽኑ የስቲሪንግና የቴክኒክ ኮሚቴዎች ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በግዢ እንዲሟሉ በማድረግ በፋብሪካዎችና ፕሮጀክቶች እያሰራጩ ነው፡፡ በተጨማሪ ፋብሪካዎችና ፕሮጀክቶች ቴክኒካል አልክሆል ከፊንጫአና መተሐራ ስኳር ፋብሪካዎች በነጻ ወስደው እንዲጠቀሙ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል፡፡

ግንዛቤን በመፍጠር ረገድም በቫይረሱ ዙሪያ በየጊዜው የሚወጡ ወቅታዊ መረጃዎች፣ የመንግሥት ውሳኔዎችና መልእክቶች የኢንደስትሪው ሠራተኞች እንዲያውቋቸው እየተደረገ ሲሆን፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራው እስከ ሠራተኞችና የአካባቢ ማኅበረሰብ መንደሮች እንዲሁም የአገዳ ቆራጮች የሚሰሩባቸው የእርሻ ማሳዎች ድረስ የሚወርድ ነው፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ መንግሥት የቫረሱን ሥርጭት በሀገር ደረጃ ለመከላከል ያወጣቸው መመሪያዎችና ያሳለፋቸው ውሳኔዎች በአግባቡ ሥራ ላይ መዋላቸውን እንዲሁም ግብዓቶች በተገቢው ሁኔታ ለየተቋማቱ በወቅቱ መድረሳቸውን የስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ በየጊዜው ክትትል የሚያደርጉ ሲሆን፣ ክፍተቶች ሲያጋጥሙም የማስተካከያ እርምጃዎች እንዲወሰዱ የሥራ መመሪያ ይሰጣሉ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በስኳር ፋብሪካዎችና ፕሮጀክቶች የኮሮና ቫይረስ በሽታ (COVID19) ምልክቶችን የሚያሳዩ ሰዎች ቢያጋጥሙ ህክምና የሚያገኙበት ማዕከል እስኪወሰዱ ድረስ ለጊዜው የሚቆዩባቸው ለይቶ ማቆያ ጣቢያዎች ተዘጋጅተዋል፡፡

ለጥንቃቄ ሲባልም በእድሜ የገፉ ሠራተኞች፣ ነፍሰጡሮች፣ ለጊዜው ያን ያህል ለሥራ ወሳኝ ያልሆኑ ሠራተኞችና ከበድ ያሉ በሽታዎች ያሉባቸው ሰዎች እረፍት እንዲወጡ ተደርጓል፡፡

በሌላ በኩል እንደ ውሃ ዋና፣ የስፖርት ማዘወተሪያና የመዝናኛ ክበባት (ከረንቡላ፣ ፑል፣ ቼዝ፣ ዳማ ወዘተ) በየተቋማቱ ተዘግተዋል፡፡ እንዲሁም በርካታ የፋብሪካዎችና ፕሮጀክቶች መግቢያና መውጫ በሮች እንዲዘጉ የተደረገ ሲሆን፣ ዋና መ/ቤትን ጨምሮ ለሥራ ክፍት በተደረጉ በሮች የሰውነት ሙቀት መለኪያ መሳሪያ/Infrared Thermometer ተዘጋጅቶ ሰዎች ሲገቡ የሙቀታቸውን መጠን መለካት ተጀምሯል፡፡

በአሁኑ ወቅት በስኳር ኮርፖሬሽን ዋና መ/ቤት፣ በስኳር ፋብሪካዎችና ፕሮጀክቶች 65 ሺህ የሚያህሉ ቋሚ፣ ጊዜያዊና ኮንትራት ሠራተኞች ይገኛሉ፡፡

Related posts