በነባር ስኳር ፋብሪካዎች የ10 ወራት ዕቅድ አፈጻጸም፣ በኮሮና ቫይረስ መከላከልና በቀጣይ ሥራዎች ዙሪያ በቪድዮ ኮንፈረንስ ውይይት ተካሄደ

በወንጂ ሸዋ፣ በመተሐራና በፊንጫአ ስኳር ፋብሪካዎች የ10 ወራት ዕቅድ አፈጻጸም፣ የፋብሪካ የክረምት ጥገናና የዝግጅት ምዕራፍ ዕቅድ እንዲሁም በኮሮና ቫይረስ መከላከል ዙሪያ ግንቦት 4/2012 ዓ.ም በቪድዮ ኮንፈረንስ ውይይት ተካሂዷል፡፡

በስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወዮ ሮባ በተመራው በዚህ ውይይት ላይ የኮርፖሬሽኑ ዋና መ/ቤት አመራሮች እንዲሁም የሦስቱም ስኳር ፋብሪካዎች ዋና ሥራ አስኪያጆችና የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት የፋብሪካዎቹ ሦስተኛ ሩብ ዓመት የምርት አፈጻጸም ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር አበረታች መሆኑን የገለጹት የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ፣ ይሁንና ከዘንድሮ ዕቅድ አኳያ ሲታይ ግን የሚቀረውን ለማሟላት በቀጣይ ጊዜያት ትኩረት ሰጥቶ መረባረብ እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡

ፋብሪካዎቹ በተቀመጠላቸው ግብ ልክ ያለመፈጸማቸው ምክንያትን ሲገልጹም፣ በመጋቢትና ሚያዝያ ወራት በፋብሪካዎቹ አካባቢ የጣለው ከባድ ዝናብ በምርት ላይ ያሳደረውን ከፍተኛ ተጽዕኖ በዋናነት ጠቅሰዋል፡፡

በዝናብ ምክንያት የተስተጓጎለውን ምርት ለማካካስም ሦስቱ ፋብሪካዎች የማካካሻ ዕቅድ በማዘጋጀትና ለዚህ ዓመት ይዘውት የነበረውን የምርት ማጠናቀቂያ ጊዜ በተቻለ መጠን በማራዘም የምርት ዕቅዳቸውን እንዲያሳኩ የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር በቀጣይ ዓመት የተሻለ ውጤት ለማምጣት እያንዳንዱ ፋብሪካ ከወዲሁ የዝግጅት ምዕራፍ ዕቅድ አዘጋጅቶ የክረምት የፋብሪካ ጥገና፣ የግብዓት አቅርቦትና ተያያዥ ሥራዎችን በተገቢው ጊዜና በተሻለ ጥራት እንዲፈጽም አቅጣጫ አመላክተዋል፡፡

በሌላ በኩል በፋብሪካዎቹ የኮሮና ቫይረስ በሽታን ለመከላከል እስካሁን በተደረገው ሰፊ እንቅስቃሴ ወረርሽኙ እንዳይከሰት ማድረግ መቻሉን ያመለከቱት አቶ ወዮ፣ በቀጣይም የተጀመረው ሁለገብ ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

በመጨረሻም በቀጣይ ጊዜያት ከሌሎቹ የስኳር ፋብሪካዎችና ፕሮጀክቶች ዋና ሥራ አስኪያጆችና አመራሮች ጋር ተመሳሳይ ውይይት እንደሚደረግ ታውቋል፡፡

Related posts