የስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ የአዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕከት

ዘመን ዘመንን እየተካ እነሆ ለ2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት ደርሰናል፡፡ በዘመናት ውስጥ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ዕድሜን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ የስኳር ኢንደስትሪ ባለፉት 65 ዓመታት በበርካታ ስኬቶችና ተግዳሮቶች ውስጥ አልፎ ዛሬ ላይ ዘርፉ ሲጀመር ወደሚታወቅበት ዝና ለመመለስ የሚያስችለውን የብሩህ ተስፋ ጉዞ ጀምሯል፡፡

በዚህ ረገድ ኮርፖሬሽናችን የኢንደስትሪውን ህልውና ለማስቀጠል የሚያስችል የአሠራር ማሻሻያ/Reform ቀርጾ ከሐምሌ 2011 ዓ.ም ጀምሮ በመተግበር የዘርፉን ስኬት ሩቅ በማይባል ጊዜ ውስጥ እውን ለማድረግ እየሰራ ይገኛል፡፡

እነሆ በዚህ መልክ ኢንደስትሪውን ከውድቀት አድኖ በውጤት ለማስቀጠል የተጀመረው ሪፎርም ገና ከጅምሩ ለስኳር የተሻለ ጊዜ እየመጣ መሆኑን አመላክቶአል ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ይህንንም በ2012 በጀት ዓመት ባስመዘገብነው አበረታች ውጤት ማረጋገጥ ችለናል፡፡

በተለይም ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ፣ የጸጥታ ችግርና የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በተከሰቱበት ሁኔታ ውስጥ ሆነን ያመረትነው 3.2 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ ስኳር ካለፉት ሁለት ዓመታት ምርት ጋር ሲነጻጸር፣ እንዲሁም ከ14.2 ሚሊዮን ሊትር በላይ ኤታኖል ካለፉት አራት ዓመታት አፈጻጸሞች ጋር ሲወዳደር በጣም ከፍተኛ ብልጫ እንዳላቸው አይተናል፡፡

ይህም ብቻ አይደለም፤ የሰው ኃይል አቅምን ለማጎልበት፣ አሠራርን ለማሻሻል፣ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ ወጪን ለመቀነስ፣ ገቢን ለማሳደግ፣ የተወዳዳሪነት መንፈስን ለመፍጠር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማምጣትና የክረምት የፋብሪካ ጥገናን በጊዜና በጥራት አጠናቆ ፋብሪካዎቹ በተያዘላቸው ጊዜ ውስጥ ወደ ምርት እንዲመለሱ ለማስቻል ያደረግነው ጥረትም በበርካታ ውጤቶች ታጅቧል፡፡

ከዚህ ባሻገር በሪፎርሙ አማካይነት ችግር የመፍታት አቅማችንን በማጎልበታችን ከአሁን ቀደም በራስ አቅም ለመጠገን የማይታሰቡ እንደ ቦይለር ሪቱቢንግ፣ ኢቫፖሬተር ፕላንት፣ አይዞሌሽን ቫልቭና የመሳሰሉ ትላልቅ ጥገናዎችን በአነስተኛ ወጪና በአጭር ጊዜ ውስጥ በተሳካ ሁኔታ ለማከናወን ችለናል፡፡ እነዚህ አፈጻጸሞችም ያቀድናቸውን እና በቀጣይም የምናቅዳቸውን ትላልቅ ግቦች ለማሳካት እንደምንችል ማሳያዎች ናቸው፡፡

 ከዚህ አኳያ ይህንን የጨበጥነውን ውጤት አጠናክረን በማስቀጠል በ2013 በጀት ዓመት      4 ሚሊዮን 732 ሺህ 487 ኩንታል ስኳርና 19 ሚሊዮን 683 ሺህ 480 ሊትር ኤታኖል ለማምረት አቅደን የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንገኛለን፡፡

 በዚህ አጋጣሚ ላስመዘገብናቸው ጅምር ውጤቶች የበኩላችሁን ድርሻ ላበረከታችሁ የስኳር ልማት ዘርፍ የሥራ ኃላፊዎች፣ ሠራተኞችና መሰረታዊ የሠራተኛ ማህበር አመራሮች እንዲሁም የኮርፖሬሽኑ የሥራ አመራር ቦርድና የባለድርሻ አካላት በስኳር ኮርፖሬሽንና በራሴ  ስም እንኳን ደስ ያላችሁ ለማለት እወዳለሁ፡፡

በመጨረሻም የጀመርነውን ለውጥ በተሻለ ሁኔታ በማስቀጠል በዘርፉ የበለጠ ውጤት አምጥተን አኩሪ ታሪክ እንደምንሰራ ጽኑ እምነቴ መሆኑን እየገለጽኩ፤ ዘመኑ የሠላም፣ የጤናና የብልጽግና እንዲሆን እመኛለሁ፡፡

መልካም አዲስ ዓመት!

Related posts