የስኳር ኮርፖሬሽን የሥራ አመራር ቦርድ የከሰምና የመተሐራ ስኳር ፋብሪካዎችን ጎበኘ

የስኳር ኮርፖሬሽን የሥራ አመራር ቦርድ የከሰምና መተሐራ ስኳር ፋብሪካዎችን ግንቦት 13/2012 ዓ.ም በመጎብኘት በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያየ፡፡

በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተርና በስኳር ኮርፖሬሽን የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ በየነ ገብረመስቀል በተመራው በዚህ ጉብኝትና ውይይት ላይ የስኳር ኮርፖሬሽን የሥራ አመራር ቦርድ አባላት፣ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ሐብታሙ ኃ/ሚካኤል እና የስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወዮ ሮባ ተገኝተዋል፡፡

በወቅቱ በፋብሪካዎቹ ከተካሄደው የመስክ ምልከታ በተጨማሪ የተቋማቱ የ10 ወራት ዕቅድ አፈጻጸም፣ የምርትና ምርታማነት ነባራዊ ሁኔታ እንዲሁም ለምርትና ምርታማነት ማነቆ የሆኑ የፋብሪካ ክፍሎች የመለዋወጫ እጥረትና ጥገና ችግሮች በፋብሪካዎቹ ዋና ሥራ አስኪያጆችና የኦፕሬሽን ዘርፎች ም/ዋና ሥራ አስኪያጆች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር የዘንድሮ አመት የምርት ማካካሻ ዕቅድ፣ የክረምት የፋብሪካና የመስክ መሳሪያዎች ጥገና ዕቅድ፤ የሙያ ሥልጠና ፍላጎት፤ የመኖሪያ ቤት፣ የመብራትና የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግሮች፣ በአካባቢዎቹ የሚከሰቱ የጸጥታ ችግሮችና አለመግባባቶች እንዲሁም የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመከላከል እየተከናወኑ የሚገኙ ሥራዎች ለውይይት ቀርበው በቦርዱ ሰብሳቢ አቶ በየነ ገብረመስቀል እና በኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወዮ ሮባ አስተያየትና የሥራ መመሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

በጉብኝቱ ማጠቃለያ የተመለከቷቸው የልማት ሥራዎች አበረታች መሆናቸውን የገለጹት አቶ በየነ ገብረመስቀል፣ የፋብሪካዎቹ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች የዘንድሮ የምርት ዕቅድን ለማሳካትና የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል እያደረጉ ያለውን ጥረት ይበልጥ አጠናክረው እንዲያስቀጥሉ አሳስበዋል፡፡ አክለውም ከአቅም በላይ የሆኑና ለጥገና ሥራ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ከማቅረብና ወሳኝ የሆኑ የፋብሪካ ክፍሎችን በመሰረታዊነት ከማደስና ከመለወጥ ጋር በተያያዘ ለተነሱ ጥያቄዎች ስኳር ኮርፖሬሽንና ቦርዱ በጋራ በመሆን የሚቻላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል፡፡

Related posts