የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የኮሮና ቫይረስ በሽታን በመከላከል ዙሪያ የሥራ መመሪያ ሰጡ

የስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወዮ ሮባ የኮሮና ቫይረስ በሽታን [COVID-19] በስኳር ኢንደስትሪ ለመከላከል የተከናወኑ ሥራዎችን አፈጻጸም ሪፖርት ካዳመጡ በኋላ የሥራ መመሪያ ሰጡ፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚው ወረርሽኙን በተቀናጀ መልክ ከመከላከል አኳያ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ዙሪያ የሥራ መመሪያ ለመስጠት ዛሬ መጋቢት 30/2012 ዓ.ም. የዋና መ/ቤት የስትሪንግና የቴክኒክ ኮሚቴዎችን እንዲሁም የማኔጅመንት አባላትን በኮርፖሬሽኑ የመሰብሰቢያ አዳራሽ አነጋግረዋል፡፡

በዚሁ ወቅት በስኳር ፋብሪካዎች፣ ፕሮጀክቶችና በስኳር ኮርፖሬሽን ዋና መ/ቤት ወረርሽኙን ለመከላከል የተከናወኑ ሥራዎች አፈጻጸም በስትሪንግ ኮሚቴው ሰብሳቢና የሰርቪስ ዘርፍ ም/ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታፈሰ አሰፋ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚው ሪፖርቱን ካዳመጡ በኋላ በስኳር ኢንደስትሪ በሽታውን ለመከላከል እየተደረገ ያለው ጥረት አበረታች መሆኑን ገልጸው፣ የተጀመረው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ በተቀናጀ የኮሚዩኒኬሽን አሠራር እንዲሁም በትክክለኛና ወቅታዊ መረጃዎች ተደራጅቶ በተጠናከረ ሁኔታ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራው እስከ ሠራተኞችና የአካባቢ ማኅበረሰብ መንደሮች እንዲሁም የአገዳ ቆራጮች የሚሰሩባቸው የእርሻ ማሳዎች ድረስ መውረድ እንደሚገባው ያስታወቁት አቶ ወዮ፣ የኮሚዩኒኬሽን ሥራውም በዋና ሥራ አስኪያጆች፣ በኮሚዩኒኬሽንና በጤና ባለሙያዎች መመራት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

የግብዓት አቅርቦትን በተመለከተ ሲገልጹም፣ ከተለያዩ አካላት በድጋፍ የተገኙና በግዢ የተሟሉ የንፅህና መጠበቂያና የመከላከያ ቁሳቁሶች በስኳር ፋብሪካዎችና ፕሮጀክቶች በአግባቡ መሰራጨታቸውንና በሚፈለገው ሁኔታ ጥቅም ላይ መዋላቸውን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል፡፡ አክለውም ከሥራ ስፋት፣ ከሠራተኛው ብዛትና እንቅስቃሴ አንጻር በተለየ ሁኔታ የበለጠ የግብዓት አቅርቦት የሚያስፈልጋቸውን ተቋማት ትኩረት ሰጥቶ መለየትና በአፋጣኝ መደገፍ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ቴክኒካል አልክሆልን በተመለከተም ፋብሪካዎችና ፕሮጀክቶች ምርቱን ከፊንጫአና መተሐራ በነጻ በመውሰድ ከglycerine እና hydrogen peroxide ጋር አዋህደው መጠቀም እንደሚችሉ አመልክተዋል፡፡

በአንዳንድ ፋብሪካዎችና ፕሮጀክቶች የሚታየውን የንፅህና መጠበቂያና የመከላከያ ቁሳቁሶች አቅርቦት ክፍተት፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግርና የመኖሪያ ቤት እጥረት (በአንድ ቤት ውስጥ በርካታ ሠራተኞች አብረው ከመኖራቸው አንጻር) አቅም በፈቀደ መልኩ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ለሚመለከታቸው የዘርፍ ም/ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡

በመጨረሻም መንግሥት የቫረሱን ሥርጭት ለመከላከል ያወጣቸው መመሪያዎችና ያሳለፋቸው ውሳኔዎች በየተቋሙ በአግባቡ ሥራ ላይ መዋላቸውን መከታተልና ክፍተቶችም ካሉ የማስተካከያ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

Related posts