የኮሮና ቫይረስ በሽታ [COVID-19] ሥርጭትን ለመከላከል የተከናወኑ ሥራዎች አፈጻጸም ተገመገመ

በስኳር ኮርፖሬሽን ዋና መ/ቤት፣ በስኳር ፋብሪካዎችና ፕሮጀክቶች የኮሮና ቫይረስ በሽታ [COVID-19] ሥርጭትን ለመከላከል መጋቢት 8/2012 ዓ.ም በዋና መ/ቤት የተቋቋሙት የስትሪንግና የቴክኒክ ኮሚቴዎች እስከ መጋቢት 25/2012 ዓ.ም ድረስ ያከናወኗቸውን ሥራዎች አፈጻጸም ገመገሙ፡፡

የሁለቱም ኮሚቴዎች ሰብሳቢዎችና አባላት በተገኙበት በዋና መ/ቤት የስብሰባ አዳራሽ መጋቢት 25/2012 ዓ.ም የተካሄደውን የአፈጻጸም ግምገማ የመሩት የስትሪንግ ኮሚቴው ሰብሳቢና የሰርቪስ ዘርፍ ም/ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታፈሰ አሰፋ ናቸው፡፡ የእለቱን ስብሰባ ሲከፍቱ እንደተናገሩት፣ ስትሪንግ ኮሚቴው የቴክኒክ ኮሚቴው ያቀረበውን ዝርዝር ተግባራትና የበጀት ጥያቄ ከመረመረ በኋላ በጀት መመደቡን እንዲሁም ከተለያዩ አካላት በድጋፍ ያገኛቸውንና በግዢ ያሟላቸውን የንፅህና መጠበቂያና የመከላከያ ቁሳቁሶች ለዋና መ/ቤት፣ ለስኳር ፋብሪካዎችና ፕሮጀክቶች በማቅረብ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

የቫረሱን ሥርጭት ለመከላከል በስኳር ፋብሪካዎችና ፕሮጀክቶች በዋና ሥራ አስኪያጆች የሚመራ አብይ ኮሚቴ መቋቋምን እንዲሁም የየዕለት ክንውኖችን የሚከታተል የቴክኒክ ኮሚቴ በሁሉም የሠራተኛ መንደሮች ተቋቁሞ የቫይረሱን ሥርጭት በተጠናከረ መልክ የመከላከል ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አቶ ታፈሰ አክለው ተናግረዋል፡፡

የመረጃ ልውውጥን ለማሳለጥ፣ ግንዛቤ ለመፍጠር፣ ቁሳቁሶችን በሚፈለገው ደረጃ ለማቅረብ እንዲሁም የክትትልና ቁጥጥር ሥራዎችን በተደራጀ መልክ ለማከናወን በአመራሩና በኮሚቴዎች ከሚከናወነው ሥራ ባሻገር በኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽንና በሠራተኛ ግንኙነትና ማኅበራዊ ጉዳዮች የሥራ ክፍሎች እንዲሁም በጤና ባለሙያዎች በኩል መረጃን ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች መፈጸማቸውንም አቶ ታፈሰ ባቀረቡት ሪፖርት ላይ ጠቁመዋል፡፡ የኮርፖሬሽኑ ከፍተኛ አመራርም በየጊዜው መመሪያዎችን በማስተላለፍና  አቅጣጫ በመስጠት ሥራዎችን እንደሚከታተል አስታውቀዋል፡፡

ለግምገማ የቀረበው የአፈጻጸም ሪፖርት እንደሚያስረዳው ለጥንቃቄ ሲባል ወደ ፋብሪካዎችና ፕሮጀክቶች ከሚወስዱ 42 መግቢያ በሮችና መንገዶች (Point of entry) አብዛኛዎቹ እንዲዘጉ ተወስኗል፡፡ እንዲሁም የመዝናኛ ቦታዎች (ፑል፣ ከረንቡላ፣ ቼዝ ወዘተ መጫወቻዎች) ተዘግተው እንዲቆዩ ተደርጓል፡፡

ከጤና ባለሙያዎች ሥልጠና፣ ከግብዓት አቅርቦትና ሥርጭት አኳያም በርካታ ተግባራት መከናወናቸው በግምገማው ታይቷል፡፡ በዚህ መሰረት እስካሁን 14,480 የፊት ማስኮች (ከዚህ ውስጥ 480ው ኤን 95 የፊት ማስኮች ናቸው)፣ 429 ቦትል አልክሆል (ሳኒታይዘር)፣ 9,000 ኤግዛሚኔሽን ግላቭ፣ 20 ጥንድ ቡትስ፣ 40 አፕረን ፕላስቲክ፣ 50 አይ ጎግል፣ 200 ባዮ ሀዛርድ ባግና 122 ሊትር ኢታኖል ተሰራጭተዋል፡፡ በተጨማሪም 3000 ሊትር ሳኒታይዘር (ባለ 1000 ኤምኤል) ለማሰራጨት ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ እንዲሁም 16 የሙቀት መለያ መሳሪያዎች የተገዙ ሲሆን፣ ሰሞኑን ለስኳር ፋብሪካዎችና ፕሮጀክቶች ይላካሉ፡፡

ከሥልጠና አኳያም ከፋብሪካዎችና ፕሮጀክቶች ለተውጣጡ 14 የጤና ባለሙያዎች በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሥልጠና አግኝተው ቴክኒካል አልክሆል፣ ሀይድሮጂን ፐርኦክሳይድና ግሪሲሊን በማቀላቀል ሳኒታይዘር ማዘጋጀት ጀምረዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ተጨማሪ አራት የጤና ባለሙያዎች በቅዱስ ጴጥሮስና ዘውዲቱ ሆስፒታሎች የቴክኒክ ሥልጠና ወስደዋል፡፡

የለይቶ ማቆያ ቦታዎች ዝግጅትን በተመለከተም በስኳር ፋብሪካዎችና ፕሮጀክቶች የኮሮና ቫይረስ በሽታ (COVID-19) ምልክቶችን የሚያሳዩ ሰዎች ሲያጋጥሙ በለይቶ ማቆያ ውስጥ እንዲቆዩ ለማድረግ ክፍሎችና የአልጋ አቅርቦቶች እየተሟሉ ናቸው፡፡ በዚህ መሰረት በፋብሪካዎችና ፕሮጀክቶች የጤና ተቋማት ውስጥ ከሚገኙ 225 አልጋዎች በተጨማሪ 366 አልጋዎችን የመያዝ አቅም ያሏቸው 30 የለይቶ ማቆያ ቦታዎች ተዘጋጅተዋል፡፡ ይህ በመሆኑም ከፋብሪካዎችና ፕሮጀክቶች በተለያዩ ጉዳዮች ወጥተው ለሚመለሱ ሰዎች ለ14 ቀናት የሚቆይበት የለይቶ ማቆያ ቦታዎች ተመቻችተዋል፡፡

በሌላ በኩል ህሙማንን ህክምና ወደሚሰጥባቸው ማዕከላት ለማጓጓዝ የሚያስችሉ አምቡላንሶችና የሌሎች ተሸከርካሪዎች አቅርቦት ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል፡፡

በራስ አቅም ከሚደረግ እንቅስቃሴ ባሻገር ከፌደራል እስከ ወረዳዎች ከሚመለከታቸው መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት እና ማኅበረሰቦች ጋር በጋራ መስራት ተጀምሯል፡፡  ከዚህ አኳያ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና ከክልሎች ጤና ተቋማት ጋር ትስስር በመፍጠር የተለያዩ ተግባራትን ለማከናወን ተችሏል፡፡

በግምገማው ማጠቃለያ ላይ እስካሁን በዋና መ/ቤት፣ በስኳር ፋብሪካዎችና ፕሮጀክቶች የተፈጸሙ ሥራዎች አበረታች መሆናቸው ተገልጾ፣ ነገር ግን በንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችና መከላከያ መሳሪያዎች ግብዓት አቅርቦትና ሥርጭት እንዲሁም የትራንስፖርት አገልግሎትን (አምቡላንስ ወዘተ) በማሟላት ረገድ የሚታዩ ክፍተቶችን በአፋጣኝ ለመፍታት ጥረት መደረግ እንዳለበት አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

Related posts