ጣና በለስ ስኳር ልማት ፕሮጀክት

ፕሮጀክቱ በአማራ ክልል አዊ ዞን ጃዊ ወረዳ ላይ የተቋቋመ ሲሆን፣ የፕሮጀክቱ ጽ/ቤትም ፋንዲቃ ከምትባለው የጃዊ ወረዳ ከተማ አጠገብ ከአዲስ አበባ በ650 ኪ.ሜ እንዲሁም ከባህር ዳር በ225 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡

በዚህ ፕሮጀክት እያንዳንዳቸው በቀን 12 ሺ ቶን አገዳ የመፍጨት አቅም ያላቸው ሁለት ስኳር ፋብሪካዎች በኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (METEC) ግንባታቸው ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም፣ በከፍተኛ የግንባታ መጓተት ምክንያት በስኳር ኮርፖሬሽንና በሜቴክ መካከል በ2004 ዓ.ም. ተደርሶ የነበረው የጣና በለስ ቁጥር 1 እና 2 ስኳር ፋብሪካዎች የግንባታ ውል እንደ ቅደም ተከተላቸው በ2010 ዓ.ም. እና 2009 ዓ.ም. በመንግሥት ውሳኔ እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡

የፋብሪካዎቹ ቀሪ የግንባታ ሥራዎች ተጠናቀው ወደ ምርት ሲገቡ በ40 ሺ ሄክታር መሬት ላይ የሚለማን የሸንኮራ አገዳ በግብዓትነት ይጠቀማሉ፡፡ ለሸንኮራ አገዳ ልማት የሚውለው የመስኖ ውሃ የሚገኘው በበለስ ወንዝ ላይ በተገነባ የውሃ መቀልበሻ ዊር አማካይነት ነው፡፡

ፋብሪካዎቹ ሙሉ የማምረት አቅማቸው ላይ ሲደርሱ እያንዳንዳቸው በዓመት 2 ሚሊዮን 420 ሺ ኩንታል ስኳር እና 20 ሚሊዮን 827 ሺ ሊትር ኢታኖል የማምረት አቅም ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ፋብሪካዎቹ የተጣራ (ሪፋይንድ) ስኳር ለማምረት ዲዛይን ከመደረጋቸው ባሻገር እያንዳንዳቸው 45 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመጨንት አቅም ሊኖራቸው እንደሚችል ታሳቢ ተደርጓል፡፡ ከዚህ አኳያ እያንዳንዱ ፋብሪካ 20 ሜጋ ዋት ለኦፕሬሽን ተጠቅሞ ቀሪውን 25 ሜጋ ዋት ወደ ብሔራዊ ግሪድ በመላክ ገቢ ያስገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡